ዓይኔን አብራልኝ |
የሕዝባችንን ችግር አብረን እንሸከም
ዓይን የሰውነት ብርሃን ናት!
ክብር ለእግዚአብሔር ይሁንና በቅርብ በተደረገው የሕዝብ ምዝገባና ኢስታትሰትክስ በተጨማሪም ከኢንተርናሸናል ኢስታትሰትክስ መረጃዎች እንደምንረዳው የሕዝባችን ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቶ በቅርቡ ከ80 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ይህን ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ስንመለከተው በረከት ነው። ‚ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ግዙአትም ‚(ዘፍ 1.28)። ጌታ ከባረከንና ካበዛን ፤ ጤንነታችንን ጠብቀንና ተረዳድተን የመኖር ኃሊፊነት ደግሞ የኃሁላችን ተግባር መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ።
ዓይን የሰውነት ብርሃን ናት!
እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ተበትነን እንድንኖርም ያደረገበት የራሱ የሆነ አላማ አለው ብዬም አስባለሁ ።በተለይም እኛ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተወልደን አዲስ ፍጥረት የሆንን ሁሉ፤ የተጠራነውና የተመረጥነው ለተለየ ዓላማ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን መጠራታችንና መመረጣችን ለራሳችን ብቻ እንደሆነ የምናስብ ከሆነ ዳግሞ የተጠራንበትን ዓላማና የጌታችንን ቃል በትክክል የተረዳን አይመስለኝም። ጌታ በወንጌል ውስጥ እንዲህ የሚል የትእዛዝ ቃል ትቶልናል፡፡ ‚ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም አሳብህም ውደድ።...ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትል ናት‛ (ማቴ 22.37-40)። በበኩሌ በዚህ ትእዛዝ መሠረት መውደድ ያለብኝ ሰውን ሁሉ ነው። ለሕዝቤ ደግሞ ድርብ ኃላፊነት የተሰጠኝ ይመስለኛል። እርስዎም ኢትዮጵያዊ ከሆኑ ለሕዝባችን ጤንነትና ብልጽግና ኃላፊነት አለብዎት ብዬ አምናለሁ።
በዚህ መሠረታዊ ነገር ላይ ከተስማማን ‘የሕዝባችንን ችግር አብረን እንሸከም’ ወደ ተባለው ፍሬ ነገር ልመለስና እንዴት ለመርዳት እንችላለን? ብለን ካሰብን መንገዱ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱን መንገድ በምሳሌ ልጠቁምዎት። ከባሕር ውስጥ እየተተፉ ውሀ አጥተው የሚሞቱ ብዙ አሶች እና በባሕሩ ወደብ ዙሪያ ለመሞት የቀረቡ ከብዙ ሺህ ባላይ የሚሆኑትን ያየ አንድ ወጣት አሶቹን ወደ ባሕር መልሶ መወርወር ጀመረ ይባላል። ታዲያ አንድ ሌላ ሰው አየውና ‘ኧረ አንተ ልጅ ለምን ትደክማለህ እነዚህን ሁሉ መልሰህ ልታድን ነው?’ ብሎ ሲጠይቀው፣ የልጁ መልስ ግን ልብ የሚነካ ነበር። ‚ኧረ አይደለም ፤ ነገር ግን የመለስኳቸው ሁሉ በሕይወት ይኖራለሉ አለው ይባላል።
መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመርዳት ባንችልም ፤ የምንችለውን ያህል ብናደርግላቸው የተረዱት ሁሉ ራሳቸውን ለመርዳት ይችላሉ። በሞራ የዓይን በሽታ ተይዘው አርሰው ለማምረት ያልቻሉትን ገበሬዎች እና ጋግረው ለመብላት ያልቻሉትን እናቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ራእይ አለን። ይሀ ራእይ ‚Fighting Blindness In Ethiopia‛ ፋይትንግ ብላይንድነስ ኢን ኢትዮጵያ ከተጀመረ አምስት ዓመት ሆኖታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በጐጃም ፤ በወለጋ ፤ በሲዳሞ እና በገሙ ጐፋ ክፍላተ ሀገራት በመሄድ በሞራ የዓይን በሽታ ለታወሩት በገጠር ለሚኖሩ ወገኖቻችን የዓይን ቀዶ ጥገና በማድረግና ጨለማቸውን ወደ ብርሃን በመለወጥ 1083 በሽተኞችን አክሟል።
ለወደፊትም ሀገሪቱን በመዞር ይህንን እርዳታ ለማድረግ እቅድ አለን። የጌታ ፈቃድ ከሆነ በመጭው ጥቅምት ወር ወደ ደምቢ ዶሎ ፤ በጥር ወር ደግሞ ወደ ወልቅጤ ለመሄድና ተመሳሳይ ሥራ ለማከናወን እቅድ አለን። ይህን ሁሉ ለማድረግ ገንዘብ ፤ የሰው ጉልበትና ብዙ የሕክምና መሣሪያዎች ያስፈልጉናል። ስለሆነም የሕዝባችን ችግር ከተሰማዎትና ለመርዳት ካሰቡ ወይም አስተያየትና ምክር መስጠት ቢፈልጉ ፤ በዚህ ዌብሳይትና አዴራሻ ሊያገኙን ይችላሉ።
ጌታ ኢየሱስ በነገር ሁሉ ይባርክዎት